በገንዳውሃ ከተማ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በገንዳውሃ ከተማ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

ገንዳውሃ፤ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ጎልቶ በሚስተዋልባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች ቀደም ሲል የመከላከያ ክትባት መጀመሩ ይታወቃል።
ይህ ስራ ከተጀመረባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ይገኝበታል።
የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሲስተር ምግብ ፈንታ እንዳመለከቱት፤ የገንዳውሃ ከተማ የወባ መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
ክትባቱ በተለይ ሕፃናትን ከበሽታው ለመታደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ክትባቱ የወባ በሽታን የመከላከል አቅም የሚጨምር መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ሌሎች ውጤታማ የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲያከናውን ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሀመድ በበኩላቸው፤ የወባ መከላከያ ክትባት መጀመሩ መንግስት የማሕበረሰቡን ጤና በዘላቂነት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የተጀመረውን የወባ በሽታ የመከላከል ስራን አጠናክሮ በማስቀጠል ጤናማና አምራች ዜጋ በመፍጠርን የብልፅግና ጉዞ ለማሳለጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ዮሴፍ ጉርባ ፤በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል ህክምና ከመስጠት ባሻገር ሕብረተሰቡ አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ በመፍጠር፣ የአካባቢ ክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።
የመከላከል ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም በመተማ ጠቅላላ ሆስፒታልና በገንዳውሃ ጤና ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ክትባቱ ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ 11 ወር ለሆኑ ሕፃናት በመደበኛነት በክትባት ጣቢያዎች የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ለአንድ ህፃን በአራት ዙር የሚሰጠው ክትባቱ የወባ በሽታን የመከላከል አቅም የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል።