በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ፍላጎት ያማከለ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር ማዕቀፍ መዘርጋት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ፍላጎት ያማከለ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር ማዕቀፍ መዘርጋት አለበት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ያማከለ ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና የልማት ፍላጎቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር ማዕቀፍ ሊዘረጋ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አመታዊ ስብሰባ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊው ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ከዓመታዊ ስብሰባው ጎን ለጎንም ፕሪኒስተን ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ስምንተኛው የዕዳ ጥናትና ምርምር የተመራጭ የብድር ሁኔታ ኮንፍረንስ ተካሄዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የዓለም የእዳ አስተዳደር ማዕቀፎች የበለጠ ግልጽነት፣ ወጥነት እና ፍትሃዊነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
ተበዳሪዎች ከአባዳሪዎች የሚያገኙት ተመራጭ የእዳ አከፋፈል ሁኔታ ላይ ግልጽ መስፈርት ባለመቀመጡ የቅርብ ጊዜ የእዳ ድርድሮች አዝጋሚ እንዲሆኑ ማድረጉንና የተገማችነት ችግሮች ያሉበት መሆኑንም አስረድተዋል።
ከተበዳሪ ሀገር አንፃር ሲታይ ደግሞ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የሚደረጉ ድርድሮችን ይበልጥ ውስብስብ እንደሚያደርገው፣ የገንዘብ ዋስትና አቅርቦትን እንደሚያዘገይ፣ በመጨረሻም የእዳ ሸክሙን ባልተመጣጠነ ሁኔታ በተበዳሪው ሀገር ላይ በመጫን ወደ ሁለትዮሽ አበዳሪዎች እንዲዘዋወር እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
ተመራጭ የብድር ሁኔታውም በግልጽ በሚታወቁናና አለማቀፋዊ መለኪያዎች በተቀመጠለት ሁኔታ የሚካሄዱ ከሆነ ፈጣን ስምምነቶችን በማድረግ በባለድርሻ አካላት መካከል መተማመንን እንደሚያመጣ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
ተመራጭ የእዳ አከፋፈል ሁኔታን የማግኘት ጉዳይ ከኢ-መደበኛ አሰራር እና ከአባዳሪዎች ማዕቀፍ ወጥቶ እንደ ቡድን 20 እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የግምገማ ማዕቀፍ ወይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፋይናንስ ሂደት ሁሉን አቀፍ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው ህጎች ተአማኒነትን እንደሚገነቡ እና የእዳ ስምምነቶችን እንደሚያፋጥኑ ገልጸው ከዛም ባሻገር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብሮችን እንደሚያጠናክሩ መናገራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።