የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርጥ የዘላቂ የደን ልማት አለም አቀፍ እውቅና አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርጥ የዘላቂ የደን ልማት አለም አቀፍ እውቅና አገኘ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርጥ የዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም በሚል ዘርፍ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እውቅና አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅናውን ያገኘችው በጣሊያን ሮም እየተካሄደ ባለው የዓለም ምግብ ጉባዔ ላይ ነው።
የዓለም የምግብ ጉባኤውም የምስረታ በዓሉ አካል ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ተሳትፈዋል።
ድርጅቱ ለኢትዮጵያ "በአረንጓዴ አሻራ ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም" በሚል ዘርፍ ዓለም አቀፍ እውቅና የሰጠ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስትን ወክለው የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ሽልማቱን ተቀብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፋኦ ርሃብን ለማጥፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር ላለፉት 80 ዓመታት የላቀ አሻራ ማሳረፉን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ዛሬ በምርጥ የዘላቂ የደን ልማትና ጥበቃ ምሳሌነት እውቅና በማግኘቱ ኮርተናል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን ተናግረዋል።
ይህ በመሪ ግልፅ ራዕይና በህዝብ ጠንካራ ተሳትፎ የተሳካና ተስፋችንን ያለመለመ ስኬት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ይህንን ተጨባጭ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲጎበኙና በዓይን አይተው እንዲመሰክሩም ጋብዘዋል።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ለረጅም ጊዜ የጸና አጋርነት ያመሰገኑት ሚኒስትሯ በጋራ ጥረታችን ችግኞችን እየተከልን የተሻለ ነገን ለልጆቻችን መገንባት ጀምረናል ብለዋል።
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና፣ በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትና በስንዴ ምርት የላቀ አፈጻጸም ላሳዩት ቁርጠኝነት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሸለሙ ይታወሳል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) 80ኛ የምስረታ ዓመት የድርጅቱን ያለፉት ዓመታት ስራዎች በሚዳስሱ እንዲሁም ቀጣይ ራዕዩን በሚገልጡ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ