ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሪፎርም እና የልማት ስራ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል-የባንኩ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሪፎርም እና የልማት ስራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ አስታወቁ።

የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊው ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካተተ ነው።

የመንግስት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ከዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ጋር ተወያይቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት ያደረገውን የረጅም ጊዜ እና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አድንቀዋል።

ባንኩ ለኢትዮጵያ ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያለው አጠቃላይ የፋይናንስ ማዕቀፍ ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሻገሩን አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት፣የወጪ ንግድ እና ሬሚታንስ እድገት፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማደግ እና የዋጋ ንረት መቀነስ በሪፎርሙ ከተገኙ ውጤቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አንስተዋል።

በውይይቱ አቶ አሕመድ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ቁልፍ የልማት የትኩረት መስኮችን አንስተዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ የሰው ሀብት ልማት ኢንቨስትመንት ማሳደግ፣ የግል የፋይናንስ ሀብት ማሰባሰብ፣ አማራጭ የፋይናንስ መፍትሄዎች መፈለግ እንዲሁም ቀጣናዊ እንዲሁም የባለብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር ሚኒስትሩ ያነሷቸው የትኩረት አጀንዳዎች ናቸው።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ፥ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት እያደረገቻቸው ያሉ ጠንካራ እና ታሪካዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን አድንቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር ያደነቁ ሲሆን ሂደቱ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ኢትዮጵያ አቅሟን ተጠቅማ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ እድገት እንድታስመዘግብ የሚያስችል ቁልፍ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ፣ የሪፎርም አጀንዳ እና የልማት የትኩረት መስኮችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሂደቱ ዘላቂ የሆነ የልማት ውጤት እንዲያመጣ ድጋፉን እንደሚያደርግ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም