በ2018 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 75 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሕበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል- ጤና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በ2018 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 75 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሕበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል- ጤና ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦በ2018 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 75 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሕበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የህብረተሰብ ጤና መድህን አባልነት አዲስ ምዝገባ፣ የነባር አባላት እድሳት እና አጠቃላይ አፈፃፀምን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢሮው የህብረተሰቡን ጤና አጠባበቅ ለማጎልበት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዋነኛው መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት፥ በመዲናዋ በ2017 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያና በሆስፒታሎች ከ2 ነጥብ 83 ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ከቀላል እስከ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ይህም ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም የነባር አባላት እድሳት በማካሄድ እና 10 በመቶ አዳዲስ አባላትን በመጨመር ከ2 ነጥብ 75 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም እስከ ህዳር 30 ቀን 2018 የሚቆይ የነባርና አዲስ የጤና መድህን አባላት ምዝገባ መጀመሩን አስረድተዋል።
መክፈል የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አቅማቸውን ባገናዘበ ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የፀደቀው የነባርና አዲስ አባል መደበኛ ዓመታዊ መዋጮ ከ1 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ 500 ብር መሆኑን ጠቅሰው የመመዝገቢያ 200 ብር መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወጪውን ከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች እና የቤተሰብ አባላት ያላቸውም በእያንዳንዱ ሰው ተጨማሪ 50 በመቶ በመክፈል አባል ማድረግ እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት፡፡
ህብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡