የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠብቀው የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ህግ የማስከበር ስራችንን እናጠናክራለን - ፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠብቀው የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ህግ የማስከበር ስራችንን እናጠናክራለን - ፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፡-በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠብቀው የዜጎች ተጠቃሚነትን የበለጠ ለማረጋገጥ ህግ የማስከበር ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት ከእንጦጦ ፓርክ እስከ አቃቂ ቃሊቲ ድረስ የተሰሩ የኮሪደር ልማት እና ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች ስራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት እንደገለጹት፤ በከተማዋ በተገነቡ መሰረተ ልማት ስራዎች እጅግ ተደንቀዋል።
በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጤና አገልግሎት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብደላ አደላ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቷ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች የሰላም ፍሬ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአገር ልማት የሚረጋገጠው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ሲሰፍን ብቻ መሆኑን ጠቁመው፤ "ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው" ብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ሰላምን የማስጠበቅና ልማትን እንዲፋጠን የማድረግ ተግባርን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል የግዥ ሃላፊ ኮማንደር ባዬ ሽፈራው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የከተማዋ ውበት፣ መሰረተ ልማቶች አገሪቷ ፈጣን እድገት ውስጥ መሆኗን አመላካቾች ናቸው።
ፖሊስ የልማት አደናቃፊ እና የፀረ ሰላም ሃይሎችን እኩይ ተግባር እያከሸፈ መምጣቱን አውስተው፤ ይህን ተግባሩን ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ የልዩ ፀረ ሽብር ኮማንዶ አባል ዋና ኢንስፔክተር አየለ አሸናፊ፤ በዛሬው ጉብኝታችን አገራችን እየተጓዘችበት ያለውን ከፍታ በተግባር ያየነበትና ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ረዳት ኢንስፔክተር ማርታ ወረቁ በበኩላቸው፤ የህዝብንና የአገርን ሰላም ለማረጋገጥ የሚከፈለው ዋጋ ለዚህ ዓይነት የልማት ስራዎች አብቅቶናል ብለዋል።
በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ተቋም ጥበቃ መምሪያ የሬጅመንት አዛዥ ኮሎኔል ማቲዮስ ሸጋው እንደገለጹት፤ ፖሊስ ህዝብና መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የራሱን አሻራ የማኖር ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡