በአፋር ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ የዲጂታል አገልግሎት ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ የዲጂታል አገልግሎት ተዘርግቷል

ሰመራ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ የዲጂታል አገልግሎት መዘርጋቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የጭፍራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዲጂታላይዝ አገልግሎት ዛሬ ወደ ስራ ገብቷል።
በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ እንደተናገሩት በክልሉ የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት በማረጋገጥ የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
የጤና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የዲጂታል መረጃ አያያዝንና የሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ መሰራቱን አክለዋል።
ይህም የጤናውን ዘርፍ በተጠናከረ መረጃ በመደገፍ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት አስተማማኝና ፈጣን ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዛሬ በይፋ ስራ የጀመረው የጭፍራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።
ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነው ይህ አገልግሎት የተደራጀ የጤና መረጃን በቀላሉ ለህክምና ተግባሩ ለማዋል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
አገልግሎቱን በቀጣይም ወደ ሌሎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የማስቀጠል ተግባር እንደሚከናወን አመላክተዋል።
የጭፍራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ አርባ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈው የሆስፒታሉ አገልግሎት መረጃን በአግባቡ በማደራጀት ግልጽነትን ከመፍጠር ባለፈ ወረፋን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።
የጭፍራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ አሚን ኡመር እንዳሉት በይፋ የተጀመረው አገልግሎት ለህክምና አሰጣጥ መቀላጠፍ፣ ለጥናትና ምርምር የተደራጁ መረጃዎችን ለማግኘት እንደ መረጃ ቋት ሆኖ ያገለግላል።
በተለይም የህክምና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ መረጃን በቀላሉ ለህክምናው ባለሞያ ተደራሽ በማድረግ ታካሚው ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ እቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።