ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅቱን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋማዊ አሰራሩን በማዘመን ወቅቱን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያበለጸገውን ዲጂታል የሰነድና ማህደር አስተዳደርና ወረቀት አልባ የአሰራር ስርዓትን (record management and smart paperless office) ዛሬ ይፋ አድርጓል።


 

ሚኒስቴሩ በወረቀት አልባ ስማርት አሰራርና የዲጂታል የሰነድ ልውውጥና አያያዝ ስርዓት ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ አንጋፋነቱን የሚመጥን በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት አልነበረውም፡፡

አሁን ላይ የተቋማዊ ሪፎርሙ አካል የሆነ የዲጂታል አሰራር ትግበራ መጀመሩን ገልጸው፥ ለዚህም ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዲጂታል ስርዓት ማልማቱን ገልጸዋል፡፡

የሰነድና ማህደር አስተዳደር ስርዓቱ በሚኒስቴሩ ከመዝገብ አያያዝ እስከ ሚሲዮኖች የመረጃ ልውውጥ ድረስ የነበረውን የወረቀት አሰራር በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት ስርዓት መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ስልጠናውም በዲጂታል የሰነድ አስተዳደር፣ በውስጥ እና በውጪ ግንኙነት እና በደብዳቤ ልውውጥ እንዲሁም በተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የጋራ አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ወቅቱን የዋጀ ስርዓት ዘመናዊ የሰነድ አያያዝ ሥርዓት ከመፍጠር ባለፈ ጊዜንና ወጪን እንደሚቆጥብ ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወሻዎች፣ ጥናቶችና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው ትልልቅ ሰነዶች የመነጩበት ተቋም መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የሶፍትዌር ስርዓቱ የተቋሙን ተሞክሮዎችና ታሪኮች በዘመናዊ መንገድ ለመሰነድ የጎላ አበርክቶ እንዳለው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ልምድና አገልግሎት ለዲፕሎማቶች ለማሸጋገር የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ ሀብትና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ጀነራል ዳንኤል ዘገዬ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ስርዓቱ የውስጥ አሰራርና የመረጃ ልውውጦችን ከወረቀት ነጻ በማድረግ በኤሌክትሮኒክ ስርዓት መሰነድ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከብሄራዊ ቤተመጻህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ወደ ዲጂታል ስርዓት የሚገቡ ሰነዶችን የመለየትና ቦታ የማስያዝ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሰንደው መያዛቸው መረጃዎችን በቀላሉ ለውሳኔ አሰጣጥ፣ ለጥናትና ምርምር ግብዓት ጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛል ብለዋል፡፡

የአሰራር ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ለተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች መሰጠት የጀመረው ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም