ቀጥታ፡

በጤናው ዘርፍ እየተተገበረ የሚገኘው የመከላከልና የማከም ፖሊሲ አበረታች ውጤት እየታየበት ነው

ባሕርዳር፤ጥቅምት 5/ 2018 (ኢዜአ)፡-በጤናው ዘርፍ እየተተገበረ የሚገኘው የመከላከልና የማከም ፖሊሲ አበረታች ውጤት እየታየበት መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማሕበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማሕበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ በጤናው ዘርፍ እየተተገበረ የሚገኘው የመከላከልና የማከም ፖሊሲ አበረታች ውጤት እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በማከም ረገድ እየተደረገ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በክልሉ ለወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ግንዛቤ የመፍጠር፣ የመከላከልና የማከም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ፥ ለወባ መራቢያነት ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው በተቀናጀ መልኩ የመከላከል ስራው ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በመሆኑም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ "የአርብ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተተገበረ ያለው የወባ መከላከል ንቅናቄ በውጤታማነት መቀጠሉን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ፥በክልሉ የወባ ስርጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የመከላከል ስራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።


 

በዚህም መሰረት ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈን፣ አጎበርን በአግባቡ የመጠቀምና መሰል የመከላከል ስራዎች እንዲሁም የሕክምና ተደራሽነትን የማከናወን ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር)፥የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚናውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

በክልሉ በተለይም ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የግንዛቤ ፈጠራ እና የመከላከል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም