ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን በማስፋት ረገድ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ለአረንጓዴ ትራንስፖርት መስፋፋት በአፍሪካ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

"በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የ2025 የአፍሪካ ኢ-ሞቢሊቲ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡


 

መድረኩ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ትራንስፖርት ትልቅ ምዕራፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ቁልፍ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በአከባቢ ጥበቃ ብሎም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት አረንጓዴ የትራንስፖርት ስርዓትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አበረታች የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የትራንስፖርት ምህዳሯን በመሠረታዊነት እየቀየረች መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጋራ አቅም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የማምረት፣ የኃይል መሙያ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት እንዲሁም ቀጣናዊ የተቀናጁ የእሴት ሰንሰለቶችን መፍጠር እንደሚቻል አመልክተዋል።

አፍሪካ ቴክኖሎጂዎችን በራሷ አቅም ለማልማት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለባት ጠቁመው፥ በትራንስፖርት ዘርፉ ዘላቂ ለውጥን ማምጣት የሚያስችል ፈጠራ ላይ የተመሰረተ የተሻለ ነገን ልንቀርጽ ይገባል ብለዋል።


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን፣ የሀገሪቱን የታዳሽ ኃይል አቅም መጠቀም የሚችል የትራንስፖርት ዘርፍ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማስፋፋት የሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት እውቅና እንደተሰጠው አመላካች መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስትራቴጂ በማጽደቅ ወደ ትግበራ ማስገባቷን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው የቀረጥ ማበረታቻ ምክንያት በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እየገቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጉባዔው የአፍሪካ ሀገራትን የብሉ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥበትም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም