ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው

ይርጋጨፌ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ የማድረግ ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በሁለተኛ ምዕራፍ የተከናወኑ የኮሪደርና የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ውብ የማድረግ ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው።

በተለይ የኮሪደር ልማት እና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች የከተሞችን ውበትና ጽዳት በማሳደግ ለኑሮ የሚመች አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ጤነኛ ዜጋን ለማፍራት እያገዘ ነው ብለዋል።

በክልሉ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በ64 ከተሞች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆነን አንስተው፤ ይህም የውስጥ አቅምን ወደ ልማት ለመለወጥ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ከተሞችን በፕላን በመምራትና የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ የተጀመሩ ልማቶችን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዞኑ ባሉ ከተሞች መሠረተ ልማትን ለማስፋፋትና አገልግሎትን ለማዘመን በተሰራው ሥራ የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየተመለሱ መምጣታቸውን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ከተሞችን በውስጥ አቅም ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚቻል ከይርጋጨፌ ከተማ ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል ገልጸው፤ በቀጣይ የከተማዋን ተሞክሮ ወደሌሎች ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

በተለይ የከተማዋን ልማት ለማጠናከር የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው የውስጥ አቅምን በማጠናከር በከተማው ልማትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለትም በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ70 ሚሊዮን ብር ወጭ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የተከናወኑ ሥራዎች፣ ሁለት ድልድዮችና አረንጓዴ ስፋራዎችን ጨምሮ ሰባት የመሠረተ ልማት ማስፋፊያዎች ለምረቃ በቅተዋል ብለዋል።


 

በከተማው መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ባለፈ አገልግሎትን በማዘመን የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መቻሉንም ከንቲባው ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም የማዘጋጃ ቤታዊ እንዲሁም የገቢና ንግድ አገልግሎቶች ዲጂታል መደረጋቸውን አንስተው፤ በቀጣይ ሁሉንም የከተማ አገልግሎቶች ከወረቀት አሰራር ነጻ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የህብርተሰብ ክፍል ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም