ቀጥታ፡

የንጋት ሐይቅ የዓሳ ምርት ለብዙዎቻችን የስራ እድል የፈጠረና ተጠቃሚም ያደረገ ነው- ወጣቶች

አሶሳ፤ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦የንጋት ሐይቅ የዓሳ ምርት ለብዙዎቻችን የስራ እድል የፈጠረና ተጠቃሚም ያደረገ መሆኑን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዓሳ በማስገር ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተንጣለለው ንጋት ሐይቅ ከ70 በላይ ደሴቶች ያሉት ትልቅ የቱሪስት መስህብ ስፍራ ሲሆን በዓሳ ምርቱም ለአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ እየሆነ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ወጣቶች በሐይቁ ላይ ዓሳ በማስገርና ለገበያ በማቅረብ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ።

በዚሁ ስራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች የንጋት ሐይቅ የዓሳ ምርት ለብዙዎቻችን የስራ እድል የፈጠረና ተጠቃሚም ያደረገን ነው ብለዋል።

በክልሉ መንጌ ወረዳ ፍርዶስ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው ዓሳ ከሚያሰግሩት ወጣቶች መካከል ሚካኤል አነጁም እና ረመዳን ሰኢድ፤ የንጋት ሐይቅ አስደናቂ የመዝናኛ ስፍራ እና የዓሳ ምርት መገኛ በመሆን ለብዙዎቻችን ጠቅሞናል በዚህም ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የሐይቁ የዓሳ ምርት በአካባቢው አዲስ የገቢ ምንጭ እና ሁነኛ የምግብ አማራጭ ሆኖ እየተሰራበት መሆኑንም ወጣቶቹ ገልጸዋል።

በክልሉ ተጠልለው የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችም ከወጣቶቹ የዓሳ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በመረከብ የምግብ ቤት በመክፈት እየሰሩ መሆኑን ተናግረው፥ በዚህም ደስተኞች ነን ብለዋል።

ከስደተኞቹ መካከል አብዱልባጊ ኑር እና ወጣት እንድሪስ አረያ፤ የህዳሴ ግድብ ከብርሃን ምንጭነቱም ባለፈ በተለይም በዓሳ ምርት ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለእኛም ጠቅሞናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በመቀበል የክፉ ቀን ወዳጅ በመሆን ላሳየው መልካምነት በማመስገን የአካባቢው ማህበረሰብም በሁሉም ነገር በጋራ እንድንጠቀም እያደረገን በመሆኑ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤታችን ሆናለች ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ የመንጌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሳላህ ራህመተላ፤ የህዳሴው ግድብ በረከቶች ብዙ መሆናቸውን አንስተው፥ በተለይም የንጋት ሐይቅ ዓሳ ደግሞ የወጣቶችን ህይወት እየቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

በወረዳው በርካታ ነዋሪዎችና በአካባቢው ተጠልለው የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችም የዓሳ ሃብቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

የንጋት ሐይቅ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የተንጣለለበት፤ከ70 በላይ ደሴቶች ያሉት እና 187 ሺህ 400 ሔክታር ስፋት ያለው መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም