ክልሎች የልማት ዕቅዶችን ወጥ በሆነ መልኩ በመፈጸም የሀገራዊ እድገትን ሊያፈጥኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎች የልማት ዕቅዶችን ወጥ በሆነ መልኩ በመፈጸም የሀገራዊ እድገትን ሊያፈጥኑ ይገባል

አሶሳ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ ክልሎች የልማት ዕቅዶችን ወጥ በሆነ መልኩ በመፈጸም ሀገራዊ እድገትን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በልማት ዕቅዶች አተገባበር ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶችን በመፈጸም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አየተመዘገበ ነው።
ለዚህም ክልሎች ያላቸውን ሀብት በተገቢው ለማልማት የሚያስችል የልማት ዕቅዶችን ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መስራታቸው የራሱ ድርሻ ነበረው ብለዋል።
ይህንን ለማቀላጠፍና የክልሎቹን የልማት ዕቅዶች የመፈጸም እቅም ወጥ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ዲጂታል መተግበሪያዎችን ሥራ ላይ እያዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰን በበኩላቸው፤ የክልሉን አቅም ያገናዘበ የልማት ዕቅድ በመተግበር ሀገራዊ ዕድገቱን ለማፋጠን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ክልሉ ከማዕድን በተጨማሪ ለእርሻ እና ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ምቹ መሆኑን ጠቅሰው ይህን በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ዲጂታል ቴክኖሎጂም የልማት ዕቅዶችን በዘመናዊ መንገድ በመከታተል ስራውን ለመምራትና ትክክለኛ ሪፖርት ለማግኘት እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።