በደሴ ከተማ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ደሴ ፤ ጥቅምት 5/2018(ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ የ2018 ሩብ የበጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በደሴ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፣ የደሴ ከተማን ለጎብኚዎቿ፣ ነዋሪዎችና ባለሃብቶች ይበልጥ ምቹና ሳቢ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
በተያዘው የበጀት ዓመትም ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ የሕብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ቀደም ብለው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲሶቹን ማፋጠን ላይ በማተኮር እንደሆነ አስረድተዋል።
ተጨማሪ የኮሪደር ልማት፣ ከመናፈሻ መገንጠያ- ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም አረብ ገንዳ የአስፋልት መንገድና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የሥራ እድል ፈጠራ፣ የገቢ አሰባሰብ፣ ገበያ ማረጋጋት፣ የመሶብ አንድ ማዕከል፣ የተማሪዎች ምገባና የመልካም አስተዳደር ስራዎችም ሌሎቹ ትኩረት የተደረገባቸው መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ዮናስ እንዳለ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሶስት ወራት ገበያውን ለማረጋጋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።
የተለያዩ የገበያ ማዕከላትን በማቋቋም ሸማቹን ማህበረሰብ ከአምራቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት የፍጆታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉን አስረድተዋል።
በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች ተስፋ ሰጭ ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ የከተማው አስተዳደር የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ተወካይና የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ምሳዬ ከድር ናቸው።
የትምህርት ቤት ማስፋፋፊያና የጤና ተቋማት ግንባታን በማከናወን የየዘርፉን ውጤታማነት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።