ቀጥታ፡

 የደመወዝ ጭማሪው የኑሮ ውድነት ጫናን የሚቀንስና የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው -የመንግስት ሠራተኞች

አርባ ምንጭ ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- መንግስት ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ የኑሮ ውድነት ጫናን የሚቀንስና የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን በአርባ ምንጭ ከተማ የተለያዩ ተቋማት የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ።

በመንግስት ይፋ የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞችን  የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ አነጋግሯል።

በአስተያየታቸውም የመንግስት የደመወዝ ጭማሪ የኑሮ ውድነት ጫናን የሚቀንስና የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ስለመሆኑ አንስተው ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የክልሉ የንግድ ቢሮ ሰራተኛ አቶ ካሣሁን ለማ፤ የደመወዝ ጭማሪው የኑሮ ውድነት ጫናን ትርጉም ባለው መልኩ የሚያቃልልና የስራ ተነሳሽነትን በማሳደግ ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።


 

መንግስት የደመወዝ ጭማሪውን ተከትሎ የገበያ ንረት ለመፍጠር የሚሞክሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ሰብለ ቢያድግልኝ፤ መንግስት ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ተገቢ እና ወቅታዊ ምላሽ የተሰጠበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመንግስት ሠራተኞች የመግዛት አቅምን የሚጨምር ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚቀንስ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው መንግስት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ህገ ወጦች ላይ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፋይናንስ ፅህፈት ቤት የሚሰሩት አቶ ስንታየሁ ሀብታሙ፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉ መንግስት የዜጎቹን ችግሮች የመፍታት ቁርጠኝነቱንና የኑሮ ውድነት ጫናን የማቃለል ጥረቱን ያሳየበት መሆኑንም ተናግረዋል። 


 

በመሆኑም የመንግስት የደመወዝ ጭማሪ የኑሮ ውድነት ጫናን የሚቀንስና የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር በመሆኑ ሁላችንም ተደስተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም