ቀጥታ፡

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ግንባታቸው የተቋረጠ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

ጊምቢ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ግንባታቸው የተቋረጠና የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ  የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መልካ በቀለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የስራ ሀላፊዎች ጋር በአካባቢው የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ምክክር አድርጓል።

የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መልካ በቀለ በወቅቱ እንዳሉት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡና የግንባታ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ የሆኑ መንገዶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት ይሰራል።


 

አሁን ላይ ግንባታቸውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ሥራ ከሚጀመርባቸው አራት መንገዶች መካከል ሁለቱ ግንባታቸው የተጓተተ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማስቀጠል መንግስት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ተናግረው የመንገዶቹን ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅም ከዞኑ አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት የነበረውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ችግር ከመፍታት ባለፈ ለህብረተሰቡ  ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ በዳሳ ዳባ፣ በዞኑ በነበረው የጸጥታ ችግርና በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተቋረጡ መንገዶችን መልሶ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡


 

በየደረጃው ያሉ የዞኑ አመራሮችም ለመንገዱ ግንባታ መፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የወረዳ አመራሮች በበኩላቸው አሁን ላይ ግንባታቸው ተጀምሮ የተቋረጡና የተጓተቱ መንገዶችን ለማጠናቅቅ በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡን የማስተባበር ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም