ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ እና የሀገራት መሪዎች በኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018(ኢዜአ):- የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና የሀገራት መሪዎች በኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ በሀዘን መልዕክታቸው ራይላ ኦዲንጋ በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበራቸውና የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና ህዝብ ተኮር የልማት ስራዎች መገለጫ ናቸው ብለዋል።

ኦዲንጋ የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት ከፍተኛ ተወካይ በነበሩበት ወቅት ለአፍሪካ የትስስር አጀንዳ መሳካት አበክረው መስራታቸውን ያወሱት ሊቀ መንበሩ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ለአህጉራዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን ስራዎች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

አፍሪካ ባለ ራዕይ ልጇን አጥታለች፤ የኦዲንጋ አሻራ የበለጸገች፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊት አህጉር የመገንባር የጋራ ጥረታችንን በጽናት እንድንቀጥል መነሳሳትን ይፈጥርልናል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ለራይላ ዲንጋ ቤተሰብ፣ ለኬንያ ህዝብና መንግስት እንዲሁም ለአፍሪካውያን በሙሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

በተመሳሳይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

በሀዘን መግለጫ መልዕክታቸውም ራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ ፓን አፍሪካዊ እና ህይወታቸውን በሙሉ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ እና ለአንድነት መታገላቸውን አውስተዋል።

ኦዲንጋ ያደረጉት የእድሜ ዘመን የነጻነት እና እኩልነት ትግል ከኬንያ አልፎም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በትውልዶች መካከል የተሻገረ እና መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ኢጋድ በዚህ ጥልቅ የሀዘን ወቅት ከኬንያ ህዝብ እና መንግስት ጋር ይቆማል ያሉት ዋና ፀሐፊው ኦዲንጋ ሁሌም የዴሞክራሲ መሰረት ለመጣል እና በአፍሪካ የነገ መለወጥ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲገነባ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሌም ሲታወሱ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

የኦዲንጋ ተምሳሌታዊ ተግባር ነጻ እና የበለጠ አንድ የሆነች አፍሪካ የመፍጠር ራዕይ የማሳካት ጉዞ አቅም ሆኖ እንደሚቀጥል አምናለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማሃሙድ እና የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በራይላ ኦዲንጋ ህልፈተ ህይወት ሀዘናቸውን ከገለጹ የሀገራት መሪዎች መካከል ይገኙበታል።

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በልብ ሕመም ምክንያት በህንድ ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው በ80 ዓመታቸው ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም