ቀጥታ፡

በሀዲያ ዞን በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዲያ ዞን በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ሀብታሙ ታደሰ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ2017/18 የመኸር ወቅት እርሻ ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል። 

ከዚህ ውስጥ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በክላስተር መልማቱን ገልጸው፣ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በዞኑ በመኸር እርሻ ከለማው መሬት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።  


 

ዕቅዱን ለማሳካት በምርት ዘመኑ የግብርና ግብአት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት መሰራቱን የገለጹት ሃላፊው፣ ምርጥ ዘርን ጨምሮ የግብአት አቅርቦቱ የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ተሰራጭቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሰብል እንክብካቤ ሥራው በተቀናጀና በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስታወቁት።  

የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ሥራው አርሶ አደሩን በማሳተፍ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት የመምሪያ ኃላፊው፣  ለዚህም የፀረ አረም መድሃኒት ከማቅረብ ባለፈ በግብርና ባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ አምቡርሴ አንጁሎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማ ሶደኖ በበኩላቸው በቀበሌው 51 አባወራዎችና እማወራዎች በክላስተር ተደራጅተው በ57 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በአሁኑ ወቅት የጤፍ ማሳቸውን በማረምና ጸረ ተባይ መድሀኒት በመርጨት እየተንከባከቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ማሳቸውን በክላስተር ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ከግብአት አቅርቦት በተጨማሪ በግብርና ባለሙያዎች ተገቢ ድጋፍና እገዛ እያገኙ ነው።

በእርሻ ሥራ ለሰብል የሚደረግ እንክብካቤ ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ጥጋቡ ሎዴቦ ናቸው።


 

በመኸር ወቅት ካለሙት ጤፍና ሌሎች ሰብሎች የተሻለ ምርት ለማግኘት በአሁኑ ወቅት የሰብል እንክብካቤ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የእንክብካቤ ሥራውን  የቤተሰብ አባላትን ጭምር በማሳተፍ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደር ጥጋቡ፣ በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አሁን ካለው የሰብሉ ቁመና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቁመው ለዚህም የሰብል እንክብካቤ ሥራቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም