ቀጥታ፡

በክልሉ ለተጀመሩ የልማት ኢንሼቲቮች ስኬታማነት የባለሃብቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- በክልሉ ለተጀመሩ የልማት ኢንሼቲቮች ስኬታማነት የባለሃብቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

በክልሉ ከሚገኙ ባለሃብቶችና የንግድ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመንግስት የልማት ኢንሼቲቮችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ  በጋምቤላ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰላም በማጽናት እንደ ሀገር የታለመውን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ ይገባል።

በክልሉ እንደ ሀገር የተጀመረውን የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማት ስራዎች ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

በተለይም በክልሉ በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ስራዎች የተሰማሩ ባለሃብቶች እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በመደገፍ ረገድ ተሳትፏቸውን እና ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማም የክልሉ ባለሃብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የልማት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ የአጋርነት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ለማስቻል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሯ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው በባለሃብቶችና በንግዱ ማህበረሰብ አባላት ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም