የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች

ገንዳ ውሃ ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአማራ ክልል የህግ የበላይነት በማስከበር የሰፈነውን ሰላም ለማፅናት ሲከናወን የቆየው ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ተግባር ውጤታማ መሆኑ ተመልክቷል።
በተሳሳተ መንገድ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ ተቀላቅለዋል።
በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ለማፅናት እየተከናወነ ባለው ተግባር እየተሳተፉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ካሉት ውስጥ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ይገኙበታል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ወዳጅ ደሳለኝ፤ በሀገራችን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ደማቅ ታሪክ እየተጻፈ ይገኛል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁላችንም በያለንበት አካባቢ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ሰላምን በማስጠበቅ የጀመርነውን ተግባር ማስቀጠል አለብን ብለዋል።
መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ እየተመለሱ ያሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የበደሉትን ሕዝብ በመካስ ሰላም ጸንቶ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ልማት እንዲጠናከር ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ብሩክ ወርቄ በበኩላቸው፤ ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።
ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ሊፀና እንደማይችል በመገንዘብ ሰላምንና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የተገኘውን ሰላም በማፅናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሰራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አለምነሽ አዛናው ናቸው።
ነዋሪዎቹ ፤የፅንፈኝነት አስተሳሰብን አጥብቀው እንደሚቃወሙ አንስተው፤ የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላምን በመጠበቅ ልማትን ለማፋጠን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የበኩላቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።