ቀጥታ፡

አዲስ የሲኒማ ኮምፕሌክስ ለሲኒማው ዘርፍ ጥራት መሻሻልና ዕድገት ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት ነው

 አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- አዲስ የሲኒማ ኮምፕሌክስ ለሲኒማው ዘርፍ ጥራት መሻሻልና ዕድገት ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ24 ሺህ ካሬ ላይ ያስገነባውን አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ትናንት ሥራ አስጀምሯል።


 

ኮምፕሌክሱ እጅግ ዘመናዊና ወቅቱ የደረሰበት ቴክኖሎጂ የተሟላለት፣ ባለ 15 ወለል ሲሆን፤ ባለ አራት ወለል የተሽከርካሪ ማቆሚያ የያዘ ነው።

በተጨማሪም 592 ህፃናትና 887 አዋቂዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የሲኒማ አዳራሾች ያለው ሲሆን፤ በቂ የሆነ የድምፅ ማስተላለፊያ ሲስተም፣ ዘመናዊ የመብራት ስርጭት፣ የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች የተሟላለት ነው።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አርቲስቶች  መካከል አርቲስት አለልኝ መኳንንት ፅጌ እንደተናገረው፤ መንግስት ኪነ ጥበብ ለሀገር እድገት ያለውን አበርክቶ በመገንዘብ እያከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ነው። 


 

ይህ እጅግ ዘመናዊ ሲኒማ ኮምፕሌክስ መገንባቱ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ቤተሰቦች ትልቅ የምስራች መሆኑን ገልጿል።

በሲኒማ ኮምፕሌክሱ ውስጥ ህጻናትን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች መካተታቸው ብቁ የሆኑ የጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ሲል ተናግሯል። 


 

አዲሱ የሲኒማ ኮምፕሌክስ የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማነቃቃት አይተኬ ሚና እንደሚጫወትም ተናግሯል።

አርቲስት ቤዛነሽ አያሌው በበኩሏ፤ አዲሱ ሲኒማ ኮምፕሌክስ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ምቾት እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሆኖ በማግኘቷ አድናቆቷን ገልጻለች።


 

ኮምፕሌክሱ ለየት ባለ መልኩ የተገነባ መሆኑን ጠቁማ፤ የተሻሉ ስራዎችን ለኪነ ጥበብ ቤተሰቦች ለማቅረብና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ያስችላል ብላለች።

ተዋናይ ደሳለኝ አሳምነው በበኩሉ በሲኒማው ውስጥ የተካተቱት መሰረተ ልማቶች መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ የተሰሩ በመሆናቸው ብቁ የሆኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት ይረዳል ብሏል።


 

የቴአትርና ኪነ ጥበብ አሰልጣኝ ሸዊት አብርሃም ደግሞ፤ የሲኒማ ኮምፕሌክስ መገንባቱ መንግስት ለዘርፉ እድገት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያረጋግጥ ተናግሯል።

አዲሱ የሲኒማ ኮምፕሌክስ መገንባቱ በኪነ ጥበብ ቤተሰብ ዘንድ መነቃቃትን እንደሚፈጥርም እንዲሁ። 


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስከረም 18 ቀን 2018 ዓ.ም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዓይነቱ የመጀመሪያ እና እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስን አስመርቆ ስራ ማስጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም