ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት ህዝብን ለልማት የማስተባበር ሀላፊነታችንን እንወጣለን-የምክር ቤት አባላት

ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- ለሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት ህዝብን ለልማት የማስተባበር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ መንግስቱ መኩሪያ እንዳሉት በክልሉ እየታዩ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጦች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው።


 

እንደ ሀገር የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችም የክልሉን ሕዝብ በልማት ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆኑ ስኬታማ እንዲሆኑ ህዝብን በማስተባበር የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሳየውን ትብብርና አንድነት አሁን ለተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችም በማሳየት የበኩሉን እንዲወጣ የማስገንዘብና የማስተባበር ሚናቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።   

ሕዝብን በአንድነት አስተባብሮ መስራት ከተቻለ የባህር በርን ጨምሮ የማይሳካ የልማት ጥያቄ አይኖርም ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ካጁ አቤል ናቸው።


 

ሀገራዊ ለውጡ እንዲጠናከርና ልማትን ለፋጠን የተጀመሩ ሜጋ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የዜጎች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ካጁ፣ ህብረተሰቡ የልማት ትብብሩን እንዲያጠናክር በሕዝብ ተወካይነታቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን መንግስት የጀመራቸው የልማት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት አርሶ አደሩ በአፈር ማዳበሪያ በየጊዜው ሲገጥመው የነበረውን ችግር እንደሚፈታ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አረጋሽ አዘዘው የተባሉ  የምክር ቤቱ አባል ናቸው።


 

የማዳበሪያ ፋብሪካውና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማስቀረት ባለፈ ምርትና ምርታማነትና በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለሀገር ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በጋራ ተረባርቦ ማሳካት እንደሚገባና ለዚህም ህዝብን ከማስተባበር  ጀምሮ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የብሔረሰቦች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱንና ክትትላቸውን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ቢልልኝ ወልደሰንበት ናቸው።


 

በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በተለያየ መንገድ ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ የህዝብን አብሮነትና የልማት ተሳትፎ ለሚያጠናክሩ ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ትናንት በቴፒ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም