ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የነባርና አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የነባርና አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ መጀመሩን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና መድህን አባልነት አዲስ ምዝገባ፣ የነባር አባላት እድሳት እና  አጠቃላይ  አፈፃፀሙን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ የህብረተሰቡን ጤና አጠባበቅ ለማጎልበት ቢሮው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዋነኛው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት፥ በመዲናዋ በ2017 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጤና ጣቢያና በሆስፒታሎች ከ2 ነጥብ 83 ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ከቀላል እስከ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። 

በ2018 ዓ.ም የነባር አባላት እድሳት በማካሄድ እና 10 በመቶ  አዳዲስ አባላትን በመጨመር ከ2 ነጥብ 75 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

ምዝገባው እስከ ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ አስረድተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የፀደቀው መደበኛ ዓመታዊ መዋጮ 2 ሺህ  ብር መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወጪውን ከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም