ተመራማሪዎች ‘Green Belt’ የሚሉት አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራማሪዎች ‘Green Belt’ የሚሉት አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙላው ሽፈራው የፓርኩን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም፤ ስለ ፓርኩ ወቅታዊ ሁኔታ እና በፓርኩ ላይ ሕገ ወጥ ተግባራት እንዳይደርስ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አንስተዋል። ከዚህ አንጻር የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበትም አብራርተዋል።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ የት ነው?
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ከአዲስ አበባ በ1ሺህ 25፣ ከባሕርዳር ደግሞ በ258 ኪሎ ሜትር ርቅት ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
በ1998 ዓ.ም የተከለለው ብሔራዊ ፓርኩ፤ 2ሺህ 666 ስኩየር ኪሎ ሜትር ወይም 266ሺህ 570 ሔክታር ስፋት እንዳለውም ገልጸዋል።
በፓርኩ ላይ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን በራስ ዐቅም ከመከወን በተጨማሪ የአካባቢውን ነዋሪ በማሳተፍ ረገድ የመከላከሉ ሥራ እንዴት እየተሠራ ነው?
በብሔራዊ ፓርኩ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራት መካከል የደን ጭፍጨፋ፣ ሕገ ወጥ አደን፣ የእንስሣት ግጦሽ፣ የእርሻ ሥራ ማስፋፋት እና ሌሎች እንደሚስተዋሉ ገልጸው በራስ ዐቅም በሬንጀሮች አማካኝነት የዕለት ተዕለት የፓትሮል ተግባራትና የአካባቢውን ነዋሪ በማሳተፍ ሕገ ወጥ ተግባራትን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አክለዋል።
በዚህም መሠረት ፓርኩን በሚያዋስኑት ሰባት ቀበሌዎች አካባቢ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የፓርኩን ጠቀሜታና የወደፊት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚመለከት ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በፓርኩ ጽሕፈት ቤት ደረጃ በስካውቶችና በሬንጀሮች የተቀናጀ ፓትሮል ፓርኩ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሙላው የፓርኩን ጥበቃና ቁጥጥር ሥራ ማጠናከር በመቻሉም፤ የዱር እንስሣቱ ፍሰት እንዲጨምር፣ የደን ጭፍጨፋ እንዳይስፋፋ ብሎም ሥነ-ምኅዳሩ በአግባቡ እንዲጠበቅ ማድረግ ተችሏል።
ማኅበረሰቡን ከፓርኩ ተጠቃሚ በማድረግ በኩልስ ምን እየተሰራ ነው?
ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የፓርክ ጥበቃ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና በርካቶች እንደ ፓርኩ ጸጋ በሕጋዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ሙላው ለአብነትም ፓርኩን ከሚያዋስኑት አንዱ በሆነው የማር ውኃ ቀበሌ 42 ወጣቶችን በሙጫ ለቀማ ሥራ በማደራጀት ገቢ እንዲያገኙ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በሌላኛው ገጽ ፓርኩን በሚያዋስነው በባንባሆ ቀበሌም አምሥት የዓሣ ማስገር እና ሦስት የንብ ማነብ ዘርፎች የተደራጁ ማኅበራት መኖራቸውን ጠቁመው በዚህም በዓሣ ማስገር ዘርፍ የተደራጁ 145 ወጣቶች ከአይማን ወንዝ ዓሣ በማውጣት ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ እንደሚገኙና ለተሻለ ነገም እየቆጠቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ወጣቶች የሥራ ባለቤት የሆኑትና ኑራቸውን የሚያስቀጥሉበት ሁኔታ የተፈጠረው የፓርኩ ኅልውና ስለተጠበቀ ነው ያሉት አቶ ሙላው አሁን ላይ ለፓርኩ ጥበቃና ቁጥጥር ሥራ አጋዥ ሆነዋል ብለዋል።
ከአካባቢው የመንግሥት አሥተዳደር ጋር በመቀናጀት ፓርኩን ለጎብኚዎች ምቹና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከማድረግ አንጻር ምን እየተሠራ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሙላው ምን ምላሽ ሰጡ?
ፓርኩ የሚገኝበት ዞን ብሎም ወረዳ እና አዋሳኝ ቀበሌዎች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ በቅርበትና በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የፓርኩን ልማት ለማሳደግ፣ ጥበቃውን ለማጠናከርና በሚፈለገው ልክ የጉብኝት መዳረሻ ሆኖ ተደማሪ የገቢ ምንጭ ለማድረግ የጋራ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት።
የፓርኩን ጥበቃና የቁጥጥር ሥራ ለማጽናት ከወረዳው በተጨማሪ የፓርኩን ልማት ከሚደግፉ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አክለዋል።
ብሔራዊ ፓርኩን በመጠበቅና ማልማት ረገድ መንግሥት እና የአካባቢው ነዋሪ በባለቤትነት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው የተሠራውን ደግሞ ለሕዝብና ለጎብኚ በማድረስ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።