የዋጋ ንረትን የሚያረጋጉ አሠራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ንረትን የሚያረጋጉ አሠራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2018(ኢዜአ)፡- 219 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ጨምሮ በአምሥት የገበያ ማዕከላት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት በበቂ ሁኔታ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አሸናፊ ብርሃኑ እንዳሉት፤ 219 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ጨምሮ በአምሥት የገበያ ማዕከላት የዋጋ ንረትን ያረጋጋ ግብይት እየተከናወነ ነው።
ለእነዚህ ገበያዎችና ማዕከላት የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት በበቂ ሁኔታ ከሥር ሥር እየቀረበ መሆኑንም ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
በየሳምንቱ እየወጣ ባለው የዋጋ ተመን መሠረት ግብይት እንደሚከናወንም አስረድተዋል።
ከሌሎች ነጻ ገበያዎች አንጻር በቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በአምሥቱ ገበያ ማዕከላት በአማካይ ከ20 በመቶ በላይ ቅናሽ ተደርጎ እንደሚሸጥም ተናግረዋል።
በሁሉም የመዲናዋ ወረዳዎች የቅዳሜና እሁድ ገበያ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከፍላጎት ማደግ አንጻር በቀጣይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን የማስፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም መሰረት አንድ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ስፍራ ባላቸው ወረዳዎች ተጨማሪ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል።
እነዚህ የገበያ አማራጮች በተቀመጠው አሠራር መፈጸማቸውን የሚከታተሉ ሱፐር ቫይዘሮች መመደባቸውን እና 1 ሺህ 216 የግብይት ተቆጣጣሪዎች በስምሪት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ሻጮች ከትስስር ውጭ እንደሚደረጉ እና በሕግም ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።