አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እና በሀገሮቻቸው መካከል ሁለንተናዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እና በሀገሮቻቸው መካከል ሁለንተናዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እና በሚወክሏቸው ሀገራት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ የተለያዩ ሀገራት አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ተቀብለዋል።
የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ አምባሳደሮች መካከል የሞሪታኒያ፣ የካዛኪስታን፣ የቫቲካን፣ የባንግላዲሽ፣ የዐረብ ሊግ፣ የኢንዶኔዥያ፣ የሰርቢያ፣ የስዊድን፣ የካናዳ፣ የሲውዘርላንድ እና የግብጽ አምባሳደሮች ይገኙበታል።
ሁነቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ አምባሳደሮቹ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደሮቹ በሥራ ዘመናቸው በኢትዮጵያና በሚወክሏቸው ሀገራት መካከል ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጎለብትና እንዲጠናከር መስራት እንዳለባቸውም አፅንኦት መስጠታቸውን ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም እያከናወነች መሆኑን ማውሳታቸውን ጠቁመው፤ አምባሳደሮቹ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተፈጠረው ምቹ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ባለሀብቶችን ማበረታታት እንዳለባቸውም እንዲሁ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያሳየች ያለው የኢኮኖሚ እና የመሰረተ ልማት እድገት በሁሉም ዘርፍ ትብብርን ለማጎልበት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድን ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ ትብብርን እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።