ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች በታሪክ የሚዘከር ታላላቅ ሥራዎች እያከናወነች ነው  - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች በታሪክ የሚዘከር ታላላቅ ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ  ገለጹ።   

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ መመስረት በአፍሪካ በጋራ የመበልጸግ ራዕይን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።   

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ሥራ የጀመረውን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa - POA) ጎብኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የለውጥ ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

በጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፣ የምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።    

አፈ ጉባኤ ታገሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች በታሪክ የሚዘከር ትልልቅ ሥራዎችን እያከናወነች ነው።   

አፍሪካ ባላት አቅም፣ ጥበብና እውቀት ልክ በዓለም ደረጃ አልተዋወቀችም ያሉት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ የአፍሪካን እምቅ አቅም የሚያሳይ የሚዲያና ተግባቦት ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

በዚህ ረገድ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች ታጥቆ ወደ ሥራ መግባቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ የአፍሪካን ትክክለኛ ገጽታ በማስተዋወቅ ለአፍሪካ ድምጽ ለመሆን ዋነኛ መንገድ ነው ብለዋል።             

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ በተለያዩ ቋንቋዎች ሥራዎችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን አስታውሰው፤ ለቀጣናዊ ትሥሥር መጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።  

በቀጣናው ዘላቂ ሠላምና እድገትን እውን ለማድረግ የተደራጀ ሚዲያና ተግባቦት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ መመስረት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።


 

የሚዲያው መመስረት በአፍሪካ በጋራ ለመበልጸግ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።  

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ የሰነቃቸው አህጉራዊ ግቦች እንዲሳኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም