ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ማምረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ማምረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ማምረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ በሀገር ውስጥ ማምረት የጀመራቸውን ድሮኖች ምርት በማስፋት የድሮን ቴክኖሎጂን በምርምር እና ሥርፀት ለማሳደግ እንዲሁም ተግባራዊ ተሞክሮን ለማዳበር የሚያግዘውን ትብብር ለመፍጠር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢፌዴሪ አየር ኃይል፣ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ ግሩፕ፣ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በመርሐ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፥ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር እንዲሁም ካለው የላቀ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂያዊ ፋይዳ አንጻር የድሮን ቴክኖሎጂን በራስ አቅም ማልማት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ተመርቆ ስራ የጀመረው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ለደኅንነት፣ ለመረጃ ስምሪት፣ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖች ምርትን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የድሮን ቴክኖሎጂ በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሲሳይ፤ እንደ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማሳለጥ እንዲሁም ወደፊት የሚቃጡ ጥቃቶችን ውጤት ከመወሰን አንፃር ያለውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በመመዘን በድሮን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆንና በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን የድሮን ቴክኖሎጂ ዐቅም ለማጎልበት የአንድ ተቋም እንቅስቃሴ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ከአምስቱ ተቋማት ጋር በትብበር እና አጋርነት ለመስራት ስምምነቱ ማስፈለጉን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ አብራርተዋል፡፡
ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ የሚያመርታቸውን ድሮኖች በዓይነትና በጥራት ለማሳደግ የድሮን ቴክኖሎጂ የሚጠቀማቸውን ስማርት ሴንሰሮች በተመለከተ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አስተዳደር፤ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዘርፉን ምርምር ውጤቶችና የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ በኩል ለውጊያ የሚውሉ ድሮኖች የሚታጠቋቸው ጦር መሳሪያዎች ምርትን፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የካበተ የአቪዬሽን ዘርፍ ተሞክሮ እንዲሁም ከኢፌዴሪ አየር ኃይል በኩል ተግባራዊ ልምምድ ለመቅሰም ታልሞ የትብበር ስምምነቱ መፈረሙ ተመልክቷል፡፡
ከመግባቢያ ሰነድ ፊርማው በኋላ የስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪና የድሮን ምርቶቹ የተጎበኙ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ እና በሀገር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ዕውቀት፣ ልምድና ሀብት በመደመር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ በትብብር ለመስራት የወሰደው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ በሚያደርጋቸው ምርምር እና ልማት እንዲሁም የሰው ኃይልን በማሰልጠን ከስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ተሞክሮ ማካፈል ብቻ ሳይሆን ወደፊት በስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ የሚመረቱ ድሮኖችን መጠቀም የሚችልበት ዕድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በዓለማችን ሀገራት ውጥረት ውስጥ በገቡ ጊዜ ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር በሚያካሄዷቸው ማናቸውም ኦፕሬሽኖች ላይ የድሮን ቴክኖሎጂ ሚናው እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት የመከላከያ ኢንጂነሪግ ኢንደስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም፤ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዘርፉን በራስ አቅም በተገቢው መንገድ ለመጠቀም በትብብር ለመስራት አጋጣሚው ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
አነስተኛ እና መካከለኛ ድሮኖችን በማምረት ስራውን የጀመረ ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንደስትሪ እ.አ.አ በ2030 ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ትላልቅ ድሮኖችን በማምረት ለዓለም ገበያ የማቅረብ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ፈጽሟል።