በሀዲያ ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የዘርፉን ስኬቶች ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀዲያ ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የዘርፉን ስኬቶች ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ በሀዲያ ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል በዘርፉ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ፡፡
የዞኑ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ መርሃ ግብር በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል፡፡
በመምሪያው የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ መሰረት አበራ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በዞኑ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
ለእንስሳት ጤና የሚሆን መኖ ከማዘጋጀት ጀምሮ ዝርያቸውን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ እየተከናወነ ባለው ዘመናዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ መርሃ ግብር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ዮሐንስ በበኩላቸው በከተማው የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ከወተት ምርት ፍላጎትና አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፈው ዓመት በተከናወነው የእንስሳት ዝርያ የማሻሻል ስራን 82 በመቶ ላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም የወተት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም በተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ በሊች አምባ ቀበሌ በእንስሳት እርባታ ላይ የተሰማሩት አቶ ዳንኤል ብርሃኑ እና በከተማው የሄጦ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ግርማ ቲርካሶ፤ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ትግበራው ውጤታማ እያደረገን ነው ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል፡፡