የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወጪ ንግድ አፈፃፀሙን ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወጪ ንግድ አፈፃፀሙን ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የወጪ ንግድ አፈፃፀሙን ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በሩብ ዓመቱ በዋና ዋና ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በሩብ ዓመቱ በወጪ ንግድ አፈጻጸም፣ በኦንላይን ንግድ ምዝገባ፣ በድህረ ፈቃድ ቁጥጥር፣ በዓለም የንግድ ድርጅት ድርድር እንዲሁም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በማስጀመር እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የወጪ ንግድን በዓይነት፣ በመጠንና በገቢ በማሳደግ፣ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር አስተማማኝ የገበያ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ክረምት እንደመሆኑ ለንግዱ ማህበረሰብ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በበጀት ዘመኑ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ 2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የወጪ ንግድ አፈፃፀምን በተመለከተ በኩራት መናገር የሚቻልበት መሆኑን ገልጸው፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 65 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 980 ሚሊዬን ዶላር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት እንደሚቻል ያሳያል ብለዋል፡፡
ይሄውም የኢትዮጵያ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የወጪ ንግድ አፈፃፀሙን ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ማድረጉን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኦንላይን ንግድ ምዝገባ ከ980 ሺህ በላይ የንግድ ፈቃድ ምዝገባና ዕድሳት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የኦንላይን ንግድ ምዝገባ 141 በመቶ አፈፃፀም መመዝገቡን በማንሳት፤ በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ የታቀደውን ሶስት ሚሊዬን ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ለማሳካት 6ኛው የሥራ ላይ የቡድን ስብሰባ ያደረገችበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከስድስት ሀገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ የገበያ ድርድር መደረጉን ተናግረዋል።
ከሌሎች ሀገራት ጋርም ቀልጣፋ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርድሩ እንደሚሳካ ተስፋ ሰጭ ምልክቶች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የብዙዎች ጥያቄ የነበረውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት መጀመር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ሩብ ዓመቱ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ተጠናክሮ የቀጠለበት መሆኑን ጠቁመው፤ አፈጻጸሙ በኢትዮጵያ ልክ ለመድረስ ከዚህ በላይ መስራት እንዳለብን አሳይቶናል ብለዋል፡፡