ለጋራ ትርክት ግንባታና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ሚናችንን ይበልጥ እናጠናክራለን- የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት - ኢዜአ አማርኛ
ለጋራ ትርክት ግንባታና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ሚናችንን ይበልጥ እናጠናክራለን- የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት

ቦንጋ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፡- ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለሚያጎለብቱ የጋራ ትርክት ግንባታና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ሚናቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት ገለጹ።
"በአጋርነት የዳበረ ኮሙኒኬሽን፤ ለሕዝብ እምነትና ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አካላት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል ።
ከተሳታፊዎቹ መካከል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ስራ አስኪያጅ ካሳሁን ወዳጆ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሀገሪቱ የተያያዘችውን ሁሉን አቀፍ የብልፅግና ጉዞ በማሳካት ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው።
በተለይም ለብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለጋራ ትርክት ግንባታ ዘርፉ ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እንዲሰራ ሚናቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የዋካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ዋኮ፤ በተለያዩ ቋንቋዎች ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትንና የጋራ ትርክት ግንባታን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ፀጋዎችን በተገቢው የማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ የገለፁት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለሙያ እየሩሳሌም አለሙ ናቸው።
ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የጋራ ትርክት ለማስረፅና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ጭምር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መብራቱ መርክኔ፤ ለብልፅግና የሚተጋና ለሕዝብ ታማኝ የሆነ የሚዲያ ባለሙያና አመራር መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዘርፉ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ጭምር ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎች ብሔራዊ ትርክትን የሚያጠናክሩ፣ አብሮነትን የሚያጎለብቱና የሀገር ብልፅግናን የሚያሳልጡ መሆን እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያም የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የዘርፉ አካላት የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።