የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ መደገፉን እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ መደገፉን እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) አመታዊ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራው ልዑክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ልዑክ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጀል ክላርክ እና ከተቋሙ የአፍሪካ የስራ ክፍል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ አጀንዳ ጋር የተሳሰረው የአይኤምኤፍ ድጋፍ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልን ያለመ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ የሪፎርሙን ሂደት እና እስከ አሁን የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን፣ ወርቅን ጨምሮ የወጪ ንግድ ገቢ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን፣ የፊሲካል ምህዳሩን ያሰፋው የግብር ማሰባሰብ አቅም ማደግ እና የኢትዮጵያ የቢዝነስ ከባቢ ሁሉን አቀፍ መሻሻልን ለአብነት ጠቅሰዋል።
አይኤምኤፍ ሪፎርሙ ካለው ግዝፈት አኳያ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያሳድግም ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ለአይኤምኤፍ ከፍተኛ አመራሮች የኢትዮጵያ መንግስት ቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ(G20 Common Framework debt treatment) ስር ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ እያደረገ ያለውን ድርድር ላይ የታዩ አዎንታዊ ለውጦችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የዕዳ ሽግሽጉ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሪፎርም ፕሮግራም ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን አመልክተው በፋይናንስ ዘርፉ ላይ እየተደረጉ ባሉ ሪፎርሞች የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶም ገለጻ አድርገዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት፣ እየተሻሻለ የመጣው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ኢኮኖሚውን ለውጭ ዘርፍ ክፍት የማድረግ ጥረቶችን ጨምሮ የታዩ ለውጦችን አድንቋል።
የአይኤምኤፍ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጀል ክላርክ የኢትዮጵያ ጠንካራ እና ድፍረት የተሞላበት የሪፎርም አጀንዳ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሆነ ገልጸው ተቋሙ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የሪፎርም ትግበራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን በውል እንደሚረዱ ገልጸው ለዚህም ዓለም ባንክን ጨምሮ ከሌሎች የልማት ፕሮግራሞች ጋር በመተባበር ተጨማሪ ሀብት ማሰባሰብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ክላርክ እ.አ.አ ዲሴምበር 2025 ላይ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውም ተመላክቷል።
ሁለቱ ወገኖች አይኤምኤፍ በአዲስ አበባ በቀጣይ የኢትዮጵያን ብድር ፕሮግራም አስመልክቶ በሚያካሂደው አራተኛ ግምገማ ላይ በቅርበት ለመስራትም ተስማማተዋል።
ግምገማው የኢትዮጵያ ሪፎርም ሂደትን በመገምገምና የሁለቱን ወገኖች ትብብር የሚያጠናክሩ ቁልፍ መስኮችን በመለየት የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ልማትና ዘላቂ እድገት መደገፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።