በአፍሪካ የመድሀኒት አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የጋራ ጥረትና አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል- ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የመድሀኒት አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የጋራ ጥረትና አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል- ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦በአፍሪካ የመድሀኒት አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የጋራ ጥረትና አቅምን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
የጤና ሚኒስቴር ከአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የአፍሪካ የመድሀኒት ግዢ ማዕቀፍ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ከዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ውይይት የአፍሪካ ሀገራት የመድሀኒት አቅራቢ ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ያላቸውን ልምድ የሚጋሩበት ነው።
በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት የህክምና ግብዓት አቅርቦትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የግዢና ቁጥጥር ስርዓትን መዘርጋት ይጠይቃል።
በተለይ ከኮቪድ 19 መከሰት በኋላ ሀገራት የህክምና ግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ ትልቅ አቅም ያላት መሆኑን አንስተው በአህጉሪቱ የሚገኙ ሀገራት ያላቸውን አቅም ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ግዢ ስርዓትን ለማሳለጥ የህግና አሰራር ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአሰራር ስርዓቶችን ከማሻሻል ባለፈ በአፍሪካ ደረጃ የጋራ ማዕቀፍ ግዢን ለመፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልፀዋል።
የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለው ዓለም አቀፍ ተደራሽነት መድኃኒቶችን ለማከፋፈል ግዙፍ አቅም መሆኑን ጠቅሰው፥ ደረጃቸውን የጠበቁ የማቆያ ማዕከሎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የሀገር ውስጥ አምራቾች አስተባባሪ ዶክተር አበበ ገነቱ ውይይቱ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የሚተገበር የጋራ የመድሀኒትና ክትባቶች የማዕቀፍ ግዢን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የግዢ ማዕቀፉን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው የዛሬው መድረክም የሀገራትን ልምድ ለመቅሰም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አህጉራዊ የግዢ ማዕቀፉን በ10 ሀገራት በመጀመር ወደሌሎች ለማስፋት መታቀዱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብድልቃድር ገልገሎ በአነስተኛ መጠን የሚፈለጉ መድሀኒቶች ግዢ ከዋጋና መጠን አንፃር ፈታኝ መሆኑን አንስተዋል።
አህጉራዊ የጋራ የማዕቀፍ ግዢ ስርዓቱ ይህን ችግር ለመፍታት የሚረዳ መሆኑን ጠቁመው፥ በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ በመድሀኒት ግዢ ያላትን ልምድ እንደምታቀርብ ተናግረዋል።