ቀጥታ፡

ዘመናዊ የሲኒማ ኮምፕሌክሱ  መንግሥት ለኪነጥበብ ማንሰራራት ያለውን ፅኑ አቋም ያረጋገጠበት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ዛሬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው አዲስ የሲኒማ ኮምፕሌክስ መንግሥት ለኪነጥበብ ማንሰራራት ያለውን ፅኑ አቋም ያረጋገጠበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ24 ሺህ ካሬ ላይ ያስገነባውን አዲስ የሲኒማ ኮምፕሌክስ መርቆ ሥራ አስጀምሯል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግሥት የኪነጥበብ ዘርፍ ለሀገር ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።


 

ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የዘርፉን ዕድገት የሚያረጋግጡ መሰረተ ልማቶችን እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ለሲኒማ ኢንዱስትሪው ምቹ ግብዓቶች እንዲሟሉ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። 

ይህም የሀገራችንን የሲኒማ ኢንዱስትሪ በዓለም አደባባይ ለማስጠራት እና እንዲተዋወቅ ያደርጋል ነው ያሉት።

ዛሬ የተመረቀው አዲስ የሲኒማ ኮምፕሌክስ እጅግ ዘመናዊና ወቅቱ የደረሰበት ቴክኖሎጂ የተሟላለት መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል። 

ይህ ዘመናዊ ኮምፕሌክስ ለዘርፉ ቀጣይ እድገት አይተኬ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።


 

የዘመናዊ የሲኒማ ኮምፕሌክሱ መገንባት መንግሥት ለኪነጥበብ ማንሰራራት ያለውን ፅኑ አቋም ያረጋገጠበት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በሲኒማ ኮምፕሌክሱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ሸዊት ሻንካ፣  የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም