ቀጥታ፡

የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ሚናውን ማጠናከር ይጠበቅበታል 

ሀዋሳ፤  ጥቅምት 4/2018 ( ኢዜአ ) :- የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማገዝ  ሚናውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ተመላከተ። 

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ  በወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተሳተፈበት መድረክ አካሄዷል።

የጤና  ቢሮው ምክትልና የሕክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በመድረኩ ላይ ፤ በክልሉ  በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይህንን  ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ  የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ግንዛቤን በመፍጠር   ዕገዛውን  እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በተለይም የወባ በሽታን ለመከላከልና የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድሕን አገልግሎት ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ዘርፉ ሚናውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። 

ቢሮው የወባ በሽታን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አካባቢን የማፅዳት፣ የኬሚካል ርጭት እንዲሁም የአልጋ አጎበር ስርጭት እና የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የአልጋ አጎበር አጠቃቀምና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎች ማሕበረሰቡ በአግባቡ እንዲተገብር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ግንዛቤን በመፍጠር የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አመልክተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢያሱ ዳዊት፣ ቢሮው እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን መዋቅሩን በመዘርጋት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዲጊሶ፣ ሕብረተሰቡ በቂ እውቀት አግኝቶ ራሱን ከበሽታ እንዲከላከል  ማስገንዘብ ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡


 

ቢሮው ከሚያከናውናቸው የግንዛቤ ሥራዎች በተጨማሪ ሰፊውን ሕብረተሰብ ተደራሽ ባደረገ መልኩ የላቀ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎች በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል ፡፡

በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን  ዘርፍ የተወጣጡ  አካላትና  ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም