ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የመምህራን ሚና ወሳኝ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የመምህራን ሚና ወሳኝ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር 23ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ተወካይና የአስተዳደርና መሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) የትምህርት ሚኒስትሩን በመወከል ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ መንግሥት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው። 

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ ለመምህራን አቅም ግንባታ፣ ሞዴል አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። 

እንዲሁም የመምህራንን ሕይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎችን ጨምሮ ተግባር ተኮር የመምህራን ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማኅበሩ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚከናወኑ ሥራዎችን በመደገፍ፣ የመምህራንን ጥቅም በማስከበር እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል፣ ግብዓቶችንና ሌሎች ክፍተቶችን ለማሟላት የትምህርት ማህበረሰቡ አካላት ርብርብ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የማኅበሩ ጠቅላላ ምርጫ በክልል ደረጃ እስከታችኛው መዋቅሮች መካሄዱን አንስተው በጉባኤው በማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ደረጃ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፤ መምህራን ትውልድን የሚቀርጹ የሀገር ባለውለታዎች መሆናቸውን እንዲሁም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በሚያከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ መምህራን በሀገር ግንባታ ሂደት  ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በአጽንዖት ጠቅሰዋል።


 

መምህራን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስልጡን ዜጋ በማፍራት ለዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለሰላምና ለልማት ስራዎች መሳካት ድርብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር  ለትምህርት ስርዓት ግንባታ፣ ለመምህራን መብትና ጥቅም፣ ለዲሞክራሲና ለሀገር ግንባታ ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

 ኮንፌዴሬሽኑ  የመምህራንን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሥራዎችን ለማጠናከር ከማኅበሩ ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

በአፍሪካ የኢዱኬሽን ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ዴኒስ ሲንዮሎ በበኩላቸው ድርጅቱ ከ400 የመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ማህበራት ጋር በ180 ሀገራት የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በአፍሪካ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ማኅበራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ መንግስታት በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን እንዲያጠናክሩ፣ የትኛውም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆንና ለመምህራንና ለተማሪዎች ምቹ ከባቢ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም