በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከ 2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከ 2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት በሩብ ዓመቱ በዋና ዋና ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በዚህም በ2018 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ 2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከፍተኛ መሻሻል የታየበት መሆኑን በማንሳት በሩብ ዓመቱ የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 65 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ የተመዘገበው የ117 በመቶ የዕቅድ አፈፃፀም በበጀት ዓመቱ የታቀደውን 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ሩብ ዓመቱ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተቃረበችበት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን የጀመረችበት መሆኑንም ተናግረዋል።