የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የአስተዳደሩ የሴክተሮችና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እየተገመገመ ይገኛል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተተገበሩ የልማት እቅዶች አበረታች ውጤት አስገኝተዋል።
በተለይ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ፈጣን ለማድረግ በተሰራው ሥራ ለተገኘው ውጤት የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የራሱ ድርሻ እንዳለው አክለዋል።
የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በቅንጅት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ከንቲባ ከድር አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩን የ2018 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እንዲሁም የሴክተሮችና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የዕቅድ ክንውን ሪፖርትን የአስተዳደሩ የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር ኃይለማርያም ዳዲ አቅርበዋል።
በሪፖርቱም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ በተደረገ ጥረት ከታክስና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች 1 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቅዳሜና እሁድ ገበያ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝብ እንዲቀርቡ ለማድረግ መቻሉንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስም ስምንት የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በገጠርና በከተማ ከ6 ሺህ 280 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን አመልክተዋል።