ስትራቴጂው በአፍሪካ ወጥነት ያለው የክህሎት ልማትን በማፋጠን አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
ስትራቴጂው በአፍሪካ ወጥነት ያለው የክህሎት ልማትን በማፋጠን አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ያግዛል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦የአፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስትራቴጂ ወጥነት ያለው የክህሎት ልማትን በማፋጠን አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት እንደሚያግዝ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ወጣቶችን እምቅ አቅም ወደ ውጤታማና ተወዳዳሪ ወደሆነ የሥራ ኃይል በመቀየር ለአህጉራዊ ሽግግር ለመጠቀም ወጥነት ያለው ክህሎት መር ፖሊሲና ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፥ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚተገበረው የአፍሪካ አህጉር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ስትራቴጂ ይፋ ተደርጓል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአፍሪካን ህዝብ በተለይም የወጣቶቿን አቅም ወደ ውጤታማ፣ አሳታፊ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወደሆነ የሥራ ኃይል መለወጥ ይገባል።
ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ማዕከል የሆነው ክህሎት ወሳኝ መሳሪያ ነው ብለዋል።
የክህሎት ልማት ለአሳታፊ ዕድገትና ለተገቢ የሥራ ዕድሎች ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ዕቅድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
እ.አ.አ ከ2025-2034 የሚተገበረው የአፍሪካ አህጉራዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስትራቴጂ ወጥነት ያለው የክህሎት ልማትን በማፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
አባል ሀገራት ብሔራዊ ዕቅዶቻቸውን ከአህጉራዊ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣም በጋራ እንዲሠሩ የሚያበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።
አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካትና በክህሎት ልማት በኩል የተሻለ፣ ፈጣን እና ይበልጥ አሳታፊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለውን የለውጥ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
የፖሊሲ ወጥነትን እና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ ክህሎቶች ለሀገራዊ ግቦችና ለአህጉራዊ የ2063 የልማት አጀንዳዎች መሳካት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለክህሎት ልማት በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው ብለዋል።
ክህሎት መር የፖሊሲ እርምጃችን ወጣቶች ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ የስራ ፈጣሪነት ባህልን በንቃት እያስተዋወቀ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ተመራቂዎች የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ እና እድገት እንዲያመጡ የሚያስፈልጋቸው ስልጠና፣ ምክር እና የገንዘብ ድጋፍ እየተመቻቸ መሆኑን አመላክተዋል።
በስልጠና ተቋማት እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።