በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማብቃት በተከናወኑት ስራዎች ውጤቶች ተገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማብቃት በተከናወኑት ስራዎች ውጤቶች ተገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018 (ኢዜአ)፡- በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማብቃት በተከናወኑ ስራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን የስፔስ ሳይንስና የጂኦስፓሻል ኢንሲቲትዩት ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቤቴልሄም ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ ባለፉት አምስት ዓመታት በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ብቁ የሆኑና በቀጣይ ቴክኖሎጂው ላይ ውጤታማ ሥራ የሚሰሩ ታዳጊዎችን ለማፍራት ሲሰራ ቆይቷል።
በዘርፉ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ለአራት ዓመታት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በስልጠናው ማጠናቀቂያ የራሳቸውን ፕሮጀክት እንዲሰሩና ስታርት አፕ እንዲጀምሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ይህ ሂደት ታዳጊዎቹ በዓለም አቀፍ ስልጠናዎችና ውድድሮች የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለ ልዩ ተሰጥኦዎችን ማፍራት አስችሏል ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ታዳጊዎቹ በፍላጎታቸው መሠረት በምርምር፣ በስታርት አፕ፣ ነፃ የትምህርት እድልና ሌሎች ዕድሎችን አግኝተው የዘርፉ ተረካቢ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢትዮ ስፔስ ኤንድ ስፓሻል ኪድስ ክለብ አስተባባሪ ኢንጂነር አልአዛር ስዩም በበኩላቸው፣ ዓለም አቀፍ ስኬት ላይ የደረሱ ሰዎች ተሰጥኦዋቸውን በሚገባ በሚደግፍ ሥርዓት አማካይነት ስኬታማ መሆን መቻላቸውን ጠቅሰው፣ ይህንኑ ተሞክሮ በሀገር ውስጥ የመተግበርን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት 411 ተማሪዎች ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ በክልሎች የስልጠናውን ተደራሽነት ለማሳደግ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ታዳጊዎች በኦንላይን ስልጠና መጀመራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ኢንጂነር አልዓዛር ስልጠና ያጠናቀቁ ተማሪዎች ፕሮጀክታቸውን በስታርት አፕ ወደ ምርት ወይም አገልግሎት እንዲቀይሩት በተመራማሪዎች እንደሚደገፉ ጠቁመዋል።
ለአብነትም፣ የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ህንፃዎች ላይ ለጽዳትና ለእሳት ማጥፊያ አገልግሎት የሚውል ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡን ሰልጣኞች መካከል የ18 ዓመቷ ሐና ጌቱ እና የ17 ዓመቱ ቶማስ በላይ፣ ስልጠናው ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
ታዳጊዎች በቀጣይ የራሳቸውን ድርጅት ለማቋቋም እና ወቅቱ የሚፈልገውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርት ለመስራት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።