ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

ደሴ ፤ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ በተያዘው ወር የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በደሴ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዲጂታል አሰራርን ለማስፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ኢዜአ የከተማ አስተዳደሩን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝን አነጋግሯል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በማብራሪያቸውም በከተማ አስተዳደሩ የህዝብን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የአገልግሎት እንግልትን ለማስቀረትና በአንድ ስፍራ ላይ በርከት ያሉ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን በተያዘው ወር አጋማሽ ላይ ለመጀመርም የግንባታ ማስተካከያ፣ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ዝግጁ የማድረግ፣ የአገልግሎት መስጫ ግብዓቶችን የማሟላትና ብቁ የሰው ሃይል ዝግጁ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በማእከሉ በተለይም የመሬት ነክ፣ ገቢዎች፣ ንግድ፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የባንክ፣ የኢሜግሬሽንና ሌሎችም አገልግሎቶች ተጀምረው እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል ብለዋል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቃሲም አበራ፤ የሕብረተሰቡን የልማትና የአገልግሎት ፍላጎቶች መሰረት ያደረጉ ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ የተቀላጠፈ ለማድረግ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲጀመር ለጊዜው በ39 የአገልግሎት አይነቶች ስራ የሚጀመር መሆኑን አንስተው አገልግሎቱ እየበዛና እየሰፋ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም