የሕዳሴው ግድብና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ሂደት መገለጫዎች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ሂደት መገለጫዎች ናቸው

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 4/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ሂደት መገለጫዎች መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የግብፅን የሀሰት ትርክትና አፍራሽነት እንቅስቃሴ በጋራ በመመከት የሀገርን ተስፋ የሰነቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በትብብርና በአብሮነት ማከናወን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ተከትሎ ሀገራዊ ፋይዳቸውን በተመለከተ ኢዜአ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን አነጋግሯል።
ምሁራኑ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከሀይል ልማት ባለፈ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ስኬታማ መሆኗንና የመፈፀም አቅሟን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ተጨባጭ ስኬት በመነሳትም ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው የኢትዮጵያ የእድገትና የማንሰራራት መገለጫዎች መሆናቸውን ምሁራኑ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደህንነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተመስገን ቶማስ፤ በኢትዮጵያ የተሳኩና በጅምር ላይ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገትና ብልጽግና ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ስለመሆናቸው አንስተዋል።
ለዚህም የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ፣ የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር በይፋ መመረቅ፣ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩ እንዲሁም ሰላማዊ የኒውክሌር ፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ካላቸው ፋይዳ ባለፈ ትርጉማቸው ላቅ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በዚህ ልክ የሚገለጽ ቢሆንም በታሪካዊ ጠላትነት የምትታወቀው ግብፅ የሀሰት ትርክትና የአፍራሽነት እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አንስተዋል።
በመሆኑም የጠላቶችንና የባንዳዎችን የጥፋት እንቅስቃሴ በጋራ በመመከት የሀገርን ተስፋ የሰነቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በትብብርና በአብሮነት ማከናወን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በቀጣናው የኢትዮጵያ የእድገት ግስጋሴ ካሰበችው በላይ የሆነባት ግብፅ በምታገኘው አጋጣሚ ሆኑ ለማደናቀፍ እየጣረች ቢሆንም በጋራ ከቆምን የማንመክተው ጠላት የማናሳካው ፕሮጀክት ሊኖር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አስራት ኤርሞሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓባይ ተፋሰስን የማስተዳደር የዘመናት የቅኝ ግዛት ትልም የነበራት ግብጽ በተፋሰሱ አገራት የትብብር (የናይል ቤዚን ኢንሸቲቭ) ስምምነት ይህ ህልሟ ላይመለስ የተቋጨ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ የዓባይ የዲፕሎማሲ ስኬት በመነሳት የባህር በር ጥያቄዋም ምላሽ አግኘቶ የሚሳካ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የባህር በር ጉዳይ የሀገርና ህዝብ ጥያቄና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግስትም በዚሁ ልክ በቁርጠኝነት እየሰራ በመሆኑ ለስኬቱ ሁላችንም ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገባል ብለዋል።