በኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን የመልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄዎች በተሻለ መልኩ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን የመልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄዎች በተሻለ መልኩ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የሕዝቡን የመልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄዎች በተሻለ መልኩ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በክልሉ የ2018 የስራ ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የመንግስትና የፓርቲ የስራ ዕቅድ ክንውን ግምገማ የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰአዳ አብዱራህማን፣ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አወሉ አብዲና በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በተገኙበት መካሄድ ጀምሯል።
በግምገማው መደረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የክልሉ አመራር በተገኙ ስኬቶች ሳይዘናጋ ቀጣይ ተልዕኮን በአግባቡ በመፈጸም የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ መዘጋጀት አለበት ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የክልሉ አመራር የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም እያደገ በመምጣቱ የሕዝቡን የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይም በክልሉ መንግስት ተቀርጸው እየተተገበሩ ያሉ የልማት ኢኒሼቲቮች በታቀደው መልኩ ውጤታማ እንዲሆኑ ርብርቡ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከልማት ስራዎች ጎን ለጎን ከቀበሌ ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊና ቀልጣፋ እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎች እንዲሰፉም ይደረጋል ብለዋል።
ዛሬ በተጀመረው መድረክም የሕዝቡን የመልካም አሰተዳደር፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎች በተሻለ መልክ መመለስ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
የሕዝብና የመንግስትን አቅም አቀናጅቶ ለማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ከማዋል አንፃር የተሰሩ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫ የመድረኩ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ተጨባጭ ውጤቶች የተገኙበት ነው ብለዋል።
የክልሉን ሰላም ከማፅናት አኳያ የፀጥታ መዋቅሩን በየደረጃው የማጠናከር ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ፤ በዚሕም ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻርም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአምስት የክልሉ ከተሞች በማስጀመር የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፍትሃዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ተሞክሯል ነው ያሉት።
ዛሬ በተጀመረው መድረክም የነበሩ ክፍተቶችን በግምገማና በአግባቡ በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ የምናስቀምጥበት ይሆናል ብለዋል።