ቀጥታ፡

ትኩረት የሚሻው የልብ ህመም

በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የጤና እክል የሚገጥማቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህም በሽታዎች መካከል የልብ ህመም አንዱ ነው።

የልብ ህመምን አስቀድሞ ለመከላከል እና ለታማሚዎችም ተገቢውን ህክምና ለማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ኢዜአ የልብ ህክምና ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ እና ኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ስንታየሁ አበበ እንደገለፁት አብዛኛው የልብ ህመም በቀላሉ አስቀድሞ መከላከል በሚቻልባቸው መንስኤዎች የሚመጣ ነው።

ለልብ በሽታ መከሰት ከሚጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የደም ግፊት፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓት እና የአካባቢን ንፅህና አለመጠበቅ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

የህፃናትና የአዋቂዎች የልብ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተር ሺቢቆም ታምራት በበኩላቸው የልብ ህመም በሰው ልጆች ላይ በተፈጥሮ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ገልፀዋል።

በተፈጥሮ ህፃናት ሲወለዱ ጤናማ የልብ አፈጣጠር ሳይኖራቸው ሲቀር ሊከሰት እንደሚችል አንስተው በስኳር ህመም፣ በማጨስና በሌሎች ጥሩ ያልሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎች ወይም በሽታዎች ሳቢያ ሊፈጠር እንደሚችል አብራርተዋል።

አንድ ሰው የልብ ህመም እንደተያዘ የሚያመለክቱ ምልክቶች መኖራቸውን በሶዶ ክርስቲያን አጠቃላይ ሆስፒታል የህፃናት የልብ ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተር ያድኤል ተገኔ ተናግረዋል።

በህፃናት ላይ የሚታዩ ምልክቶች ጡት በሚጠቡበት ወቅት ላብ ማላብ እንዲሁም በሽታው ስር ከሰደደ የማቃሰት ሁኔታ እንደሚኖር በማንሳት እነዚህ ምልክቶች የልብ ችግርን ሊያሳዩ ስለሚችሉ መመርመር ተገቢ ነው ብለዋል።

በአዋቂዎች ላይ ደግሞ የድካም ስሜትና የሰውነት ማበጥ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎቹ የልብ ህመምን አስቀድሞ ለመከላከል ማህበረሰቡ ሊያጎለብታቸው የሚገቡ ልማዶችን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ለልብ በሽታ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች መቆጠብ፣ አመጋገብን ማስተካከል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ህመሙ በተለያዩ ምክንያቶች ሲያጋጥም ችላ ሳይባል ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና መውሰድ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

በተፈጥሮ የሚመጡ ከልብ ጋር የተገናኙ በሽታዎችን ለመከላከል ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ወቅትና በኋላ ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ ጤናማ ልጅ መውለድ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በተጨማሪም፣ የልብ ህመም ህክምና ለሚሹ ወገኖች በስፋት ለመድረስ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ሚና እንዲጎለብትም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም