ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን ለማስፋት በፖሊሲ የተደገፈ እርምጃ እየወሰደች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን ለማስፋት በፖሊሲ የተደገፈ እርምጃ እየወሰደች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን ለማስፋት በፖሊሲ የተደገፈ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በአረንጓዴ ትራንስፖርትና በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች የአዳማ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን፣ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰንን ጨምሮ ከኢትዮጵያ እና ኬንያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የትራንስፖርት ዘርፉን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ባከናወነቻቸው ተግባራት በርካታ ለውጦችን አስመዝግባለች ብለዋል፡፡
ለዚህም በሕዳሴ ግድብ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርና በንፋስ ኃይል ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ትልቅ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅና ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የጸዳ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
መንግሥት ታዳሽ ኃይል የሚጠቀም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍን እውን ለማድረግ ጠንካራ የፖሊሲ ድጋፍ ስለማድረጉ አንስተዋል።
በዚህም በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን በማንሳት፥ ባለሀብቶችም በዘርፉ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና መንግስት በአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት የተሰማሩ ተቋማትን እንደሚያበረታታ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለዓለም ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይ ደግሞ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የወሰደው እርምጃ ይበል የሚባል ነው ብለዋል፡፡
ሀገራቸው ይህንን ተግባር እንደምትደግፍም አረጋግጠዋል፡፡
የአፍሪካ ኢ-ሞቢሊቲ ሳምንት ከነገ ጥቅምት 4 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2018 በአዲስ አበባ ይካሔዳል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የብዙሃን ትራንፖርት፣ ባቡር፣ ኮሪደር ልማት፣ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች እንዲሁም በፖሊሲ ረገድ እያከናወነች ያለችውን ተጨባጭ ሥራ እንደምታቀርብም ተገልጿል።