የኢትዮጵያ ጉዞ ዓለም በሚያየውና በሚመሰክረው ሀገራዊ ስኬት የተደገፈ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጉዞ ዓለም በሚያየውና በሚመሰክረው ሀገራዊ ስኬት የተደገፈ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉዞ በምኞት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ዓለም በሚያየው፣ በሚዳስሰውና በሚመሰክርላቸው ስኬቶች የተደገፈ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ’’ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ፍቅር፣ ክብርና ቃል ኪዳን በልባቸው የሚያድሱበት የጋራ ማንነታቸውን የሚያጎለብቱበትና የነገ ተስፋን የሚያጸኑበት ነው ብለዋል።
ክብረ በዓሉ ያለፈውን የጀግንነት ገድል፣ የዛሬውን የልማት ጥረት፣ የነገውን የዕድገትና ብልጽግና ትልም በማጣመር ፈጣን ዕድገት ለምታስመዘግበው ኢትዮጵያ ድል አብሳሪና የጉዞ ህያው ምስክር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን የህልውና ፈተናዎች በህዝቦቿ የአንድነት ብርቱ ክንድ በጽናት ተሻግራ የራሷን ዕድል የመወሰን ብቃት እያስመሰከረች መሆኗንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ጉዞ በምኞት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ዓለም በሚያየውና በሚዳስሰው ብሎም በሚመሰክርላቸው ሀገራዊ ስኬቶች የተደገፈ ነው ብለዋል።
የዚህ ብስራት መቅረዝና ከፍታም የዘመናት ህልም የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ የሀገርንና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ የደም ስር ለመሆን መብቃቱን ገልጸዋል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከብርሃን ምንጭነት ባሻገር ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ገድሎችን ማስመዝገብ እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት የሉዓላዊነት ማህተም መሆኑን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መትከሏን አስታውሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየርና ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ በማበርከት ዓለም አቀፍ ከበሬታና ሞገስ ያስገኘላት የልማት ገድል ነው ብለዋል።
የዕድገት ጉዟችን ቀጣይ ምዕራፍ የኢኮኖሚ ብርታትን ማረጋገጥ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውም በግብርና ምርታማነት የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከውጭ ከሚገባ የማዳበሪ ጥገኝነት በማላቀቅ ሀገራዊ ኢኮኖሚን የሚያጠናክር ታላቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ ሃብትን በመጠቀም ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለኃይል ምንጭነት እንዲውል የማድረግ ውጥንም በአዲስ የኃይል ምንጭ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ጉዞን እንደሚያፋጥን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩና የሀገርን የከፍታ ዘመን በማይናወጥ መሠረት ለማስቀመጥ እንደሚረዱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ውጤታማነት ለማስቀጠልም በልዩነት ውስጥ ያለን ወርቃማ ውበት በማክበር የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ሰላም መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚከበረው በጠንካራ አንድነትና በበለጸገ ኢኮኖሚ ላይ ማቆም ሲቻል እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ለዚህም ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘትና የመጠቀም መብታችን በሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ማስከበራችን ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንም በአዕምሯቸው ሰላምን በማጽናት በልባቸው የተስፋ ወጋገን አጥብቆ በመያዝ በክንዳቸው ብርታትም ሠንደቅ ዓላማና ሀገራቸውን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።