የኢትዮጵያ ኢኖቬተሮች እና ስራ ፈጣሪዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሁነት በዱባይ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኖቬተሮች እና ስራ ፈጣሪዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሁነት በዱባይ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- 45ኛው የገልፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ (ጂአይቴክስ) ዛሬ በዱባይ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ተጀምሯል።
“የዳታ ማዕከላት በነገ ዲጂታል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ውስጥ ያላቸው ቁልፍ ሚና” የአውደ ርዕዩ መሪ ሀሳብ ነው።
በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉት የቴክኖሎጂ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ጀማሪ ስራ ፈጠራ ትዕይንቶች አንዱ በሆነው ጂአይቴክስ ከ180 ሀገራት የተወጣጡ ከ6 ሺህ 500 በላይ አቅራቢዎች፣ 1 ሺህ 800 ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች እና 1 ሺህ 200 ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ጂአይቴክስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ኢኖቬተሮች እና ተመራማሪዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘ ነው።
ዓለም አቀፍ አውደ ርዕዩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ የጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ኢኖቬሽን፣ የጤና እና ባዮ ቴክኖሎጂዎች፣ ኮሙኒኬሽን፣ ሮቦቲክስ፣ የቀጣዩ ትውልድ ቴክኖሎጂዎች፣ የኮምፒዩተር ስርዓቶች እና ማሽኖችን ጨምሮ በርካታ ዘርፎችን ይዟል።
በጂአይቴክስ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ኢኖቬተሮች እና ባለሀብቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ Pulse of Africa ሚዲያ ከስፍራው ዘግቧል።
እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው ዓለም አቀፍ ሁነት በዋናነት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ መሰረት ያደረጉ ፈጠራዎች እንደሚቀርቡና በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተመላክቷል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ጉባዔ (አንክታድ) ጥናት ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2033 የሰው ሰራሽ አስተውሎት ገበያ ወደ 4 ነጥብ 8 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን ላይ የ757 ነጥብ 58 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ድርሻ እንዳለው ይገመታል።
አንክታድ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቴክኖሎጂ ገበያው ያለው ድርሻ ወደ 29 በመቶ ማደጉን ጠቅሶ፤ ይህም ኤአይ በዘርፉ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ አቅም የሚያመላክት ነው።
ይህ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቀጣይ ጊዜያት በዓለም ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ ያሳያል።
የገልፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ (ጂአይቴክስ) እ.አ.አ 1981 አንስቶ እየተካሄደ የሚገኝ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ሁነት ነው።