ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ግልጽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ችሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ተግባር ይጠናከራል-የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ባህር ዳር፤ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)-በአማራ ክልል ግልጽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ችሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ተግባር  ተጠናከሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

በክልሉ በክረምት የዳኞች የእረፍት ጊዜ ምክንያት ዝግ ሁኖ የቆየው የችሎት አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አደራ በችሎት አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ ስርአት ላይ እንደገለጹት፣ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት አገልግልት ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል።


 

በፍርድ ቤቶች የሚሰጠው መደበኛ የችሎት ተግባር ቀልጣፋ እንዲሆን ባለፈው ዓመት በዲጂታል የታገዘ የችሎት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፤ አገልግሎቱም የተገልጋዩን ገንዘብ፣ ወጪና እንግልት ይቀንሳል ብለዋል።

በዲጂታል የታገዘ የችሎት ሥራን በማስፋፋት የተገልጋይን ጊዜ፣ ወጪና ገንዘብ ለመቀነስ የተጀመረው ተግባር በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክረምት ወቅት በተካሄደ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የዲጂታል ችሎትን በተሟላ መልኩ ለማስኬድ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም አውስተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የእድሳት ሥራ የተከናወነለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻ የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋና ጊዜውን የሚመጥን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አቶ ሀብታሙ አስገንዝበዋል።

ዲጂታል አሰራሩ ባለጉዳዮች ዞን በሚገኙ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሆነው ወደክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይመጡ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት የሚያገኙበት ስርአት ለመዘርጋት መቻሉንም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ህብረተሰቡ  ነጻ፣ግልጽና ተአማኒነት ያለው ፍትህ አግኝቶ እርካታን ለመፍጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም