የሰንደቅ ዓላማውን ክብር በሚመጥን የስራ ትጋት የበለፀገችና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ ዓላማውን ክብር በሚመጥን የስራ ትጋት የበለፀገችና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይገባል

አርባ ምንጭ፣ዲላ፣ ቦንጋ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ) :- የሰንደቅ ዓላማውን ክብር በሚመጥን የስራ ትጋት የበለፀገችና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ ተመላከተ።
18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ ሐሳብ በቦንጋ፣ ዲላና አርባ ምንጭ ከተሞች በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
በቦንጋ ከተማ በተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይ መልእክት ያስተላለፉት የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ግርማ ደፋር የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር በየዘመኑ ለሀገር ነፃነትና ክብር የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትና የነፃነት ምልክት መሆኑን ጠቅሰው ክብሩን በሚመጥን የስራ ትጋት በርትቶ በመስራት የበለፀገችና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ሰነድ ያቀረቡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ለሰንደቅ ዓላማ ከፍታ የተከፈለው ዋጋ የማይረሳና በየዘመኑ እየተዘከረ የሚኖር መሆኑን ገልፀዋል።
የቀኑ መከበር ሀገራዊ እሴቶችን አጠናክሮ ለትውልድ በማስተላለፍ አንድነታችንንና ህብረታችንን በማጠናከር ህብረ-ብሔራዊነትን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፣ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክትና የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን አንስተው ቀኑ ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ በሰፊው መከበር እንዳለበት አንስተዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወላይቴ ቢቶ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መለያ፣ የሉዓላዊነትና የአንድነታችን መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
የሃገሪቱን የማንሠራራት ጉዞ ለማስቀጠልም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይም በዲላ ከተማ በዓሉ ሲከበር የጌዴኦ ዞን ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ምስጋና ዋቃዮ እንዳሉት ቀኑ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለውና ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው።
የህብረ ብሔራዊትንና ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ማክበርና ማጉላት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የሃገራችን ኩራትና ነጻነት በመሆኑ የሚገባውን ክብር ልንሰጠው ይገባል ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የሰንደቅ ዓላማ ክብርን ማጎልበት እንደሚገባም አንስተዋል።