ቀጥታ፡

በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - አቶ አብርሃም ማርሻሎ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ገለፁ።

የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ባካሄደው የሴክተር ጉባኤ አቶ አብርሃም እንደገለጹት በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጎልበት የዜጎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

‎በዚህም በተለይ ወጣቶች ተወዳዳሪ በመሆንና የተሻለ ሀብት በመፍጠር ረገድ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ነው  የገለጹት።

‎የአካባቢን የልማት አቅም በመለየትና ወጣቶችን በቂ ክህሎት በማስጨበጥ እሴት በሚጨምሩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መደላድል የመፍጠር ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

በጉባኤው የተገኙት ሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው እንዳሉት እንደ ሀገር ብቁ የሰው ኃይል በማፍራትና ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።


 

ክህሎት መር በሆነ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ እንዲሁም በተቋም ግንባታ ላይ የሪፎርም አጀንዳዎችን በመቅረጽ የተለያዩ ሥራዎች እተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በዚህም ላለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት በአማካይ በዓመት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ ከ2015 ዓ.ም በፊት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው ክህሎትን ዋንኛ ትኩረት ያደረገ ባለመሆኑ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት ሳይመዘገብ ቆይቷል። 


 

ባለፉት ሁለት ዓመታት አንድም ዜጋ ያለ በቂ ክህሎትና ሥልጠና ወደሥራ እንዳይገባ አቅጣጫ ተቀምጦ ሲሰራ መቆየቱንም አመልክተዋል፡፡

ይህም ቀደም ሲል  የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ላይ ይስተዋል የነበረው የውጤት ማጣት፣ የመበተን፣ የመሰላቸት እና ሀብት መፍጠር ያለመቻል ችግር ተፈትቶ ውጤት መታየት መጀመሩን ገልጸዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለፃ በ2017 በጀት ዓመት በመደበኛ ሥልጠና ከ30 ሺህ በላይ እንዲሁም በአጫጭርና ገበያ ተኮር ሥልጠናዎች ከ61 ሺህ በላይ ዜጎችን ማሰልጠን ተችሏል ፡፡ 

በሥልጠና ተቋማት፣ በአገልግሎት መስጫ እና በሥራ ማዕከላት ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዐትን በመዘርጋትም ዘርፉን የማዘመን ሥራም ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

በመድረኩ በተያዘው ዓመት በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማትና አጋር አካላት የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም